ኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከአዋሽ ባንክ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

ኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከአዋሽ ባንክ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።
የጋራ ስምምነቱን የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ምስጋኑ አርጋ(አምባሳደር) እና የአዋሽ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፀሀይ ሽፈራው ተፈራርመዋል።
የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፀሀይ ሽፈራው ስምምነቱ የሁለቱን ተቋማት ግንኙነት በማጠናከር የብድርና የውጭ ምንዛሬ በማመቻቸት ተቋሙ በሚገኝበት ቦታዎች ሁሉ አገልግሎቱን በማስፋፋት የስራ የግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል።
በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያቀላጥፍ ስራ አስኪያጅ የተመደበ ሲሆን አስፈላጊ ሲሆን በግሩፑ ስር ባሉ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ቅርንጫፎችን የመክፈት ፣ኤ ቲ ኤሞችን የመትከልና ለግሩፑ የበለጠ ተደራሽ ለመሆን የሚችልበት አሰራርም በስምምነት ውስጥ የተካተተ ነው፡፡
ላለፉት ሀያ ስምንት አመታት በሀገሪቱ የግል ባንኮች ዘርፍ ፈር ቀዳጅ የሆነው ባንኩ በ2022 በግሎባል ባንክ ዘርፍ ተሸላሚ መሆኑን አንስተው በቀጣይም ከግሩፑ ጋር ለጀመሩት ስራ መሳካት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል።
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ምስጋኑ አርጋ(አምባሳደር) ግሩፑ በተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ላይ የተሰማራ በመሆኑ እንደ ሃገር የተከሰተው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ግሩፑንም እየፈተነው መሆኑን አንስተዋል፡፡ በመሆኑም ባንኩ የውጭ ምንዛሬ ምደባ በማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ግሩፑ ሰፊ የማምረት አቅም ያለው መሆኑንም በማንሳት በጋራ የተጠቃሚነት መርህ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎትና ቁርጠኝነትም አንጸባርቀዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ ከተቋሙ ባሻገር የግሩፑ ማኔጅመንት ሰራተኞች በተመጣጣኝ ወለድ ብድር የሚያገኙበትም አሰራር ያካተተ ነው፡፡
በፊርማ ስነ-ስርአቱ ላይ የኢትዮ -ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የሀብት ዘርፍ ም/ዋ/ስ/አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ገ/ማርያምን ጨምሮ ከፍተኛ ሀላፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ በአዋሽ ባንክ በኩል የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ዲባባ ጨምሮ ከፍተኛ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *