ኢትዮ ኢንጂነሪግ ግሩፕ ከኢ ኤል ኔት ግሩፕ ጋር አውቶሞቢሎችን ለመገጣጠም የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እና የኢ ኤል ኔት ግሩፕ ፕሬዝዳንት ቶኪቻ አለማየሁ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡
በስምምነቱ መሰረት ከ3 ሺህ እስከ 5 ሺህ የሚደርሱ የቤት አውቶሞቢሎች በኤስ ኬ ዲ ይመረታሉ፡፡
ኢ ኤል ኔት ግብአቶችን በማቅረብ በርካታ ሰራተኞች ባሉት በግሩፑ ስር በሚገኘው የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪ አውቶሞቢሎቹ ይገጣጠማሉ፡፡
በስምምነቱ ወቅት የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እንዳሉት የሃገር ውስጥ ኩባንያዎች በመተባበር ያላቸውን አቅም በጋራ ከተጠቀሙ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ ይችላሉ፡፡
አምባሳደር ሱሌይማን አክለውም ያሉትን አቅሞች በማሳደግ ከመገጣጠም ወደ ማምረት ደረጃ በደረጃ መሸጋገር እንደሚገባም ያመለከቱ ሲሆን የሃገር ውስጥ ኩባንያዎች ከመወዳደር ባሻገር መተባበርንም ታሳቢ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የኢ ኤል ኔት ግሩፕ ፕሬዝዳንት ቶኪቻ አለማየሁ (ኢንጂነር) በበኩላቸው ሰፊ የማምረት አቅም ካለው ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ጋር በጋራ ለመስራት በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ሰራተኞችም አውቶሞቢሎቹን የመገጣጠም ስልጠናዎችን ይወስዳሉ፡፡
ኢ ኤል ኔት ግሩፕ በድሬደዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ዞን ውስጥ የሚገኝ ኩባንያ ሲሆን 3 ሺህ አውቶሞቢሎችን በመገጣጠም ወደ ኢኮኖሚው ያስገባ ኩባንያ ነው፡፡
