ስምምነቱን የግሩፑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እንዲሁም በ ካፔድ በኩል የማህበሩ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ሎሬት ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ ተፈራርመዋል።
በስምምነቱም መሠረት ግሩፑ እንደ ዊልቸር፣የእጅ ክራንች የአይነ ስውራን ዘንግ እና ሌሎች መገልገያ መሳሪያዎችን ለመጠገንና ለማምረት የሚያስችል ነው።
የማህበሩ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ሎሬት ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ መገልገያ መሳሪያዎቹን በብዙ ወጪ እና እንግልት ከሌሎች ሀገራት እንደሚገቡ ገልፀው ለወደፊቱ ከግሩፑ ጋር በገቡት ስምምነት እነዚህን ችግሮች እንደሚቀንሱ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ አካል ጉዳተኞች የማህበረሰቡ አካል በመሆናቸው ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልፀው፤ ለዚህም በስምምነቱ መሰረት በተግባር ልናደርገው ቁርጠኛ ነን ብለዋል።
በእለቱም የግሩፑ ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ የማህበሩ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገ/መድህን ገ/ስላሴ፣የፐርፐስ ብላክ ኢትዮጵያ፣የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢንሹራንስ ተወካዮች ተገኝተዋል።