ታህሳስ 2/2018 አ.ም (ኢኢግ) ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕና ኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ውይይይትና የስራ ጉብኝት አካሄዱ፡፡
የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ አመራሮች በግሩፑ ስር የሚገኙትን አዲስ ማሽንና መለዋወጫ ማምረቻ ኢንዱስትሪን እና ኢትዮጵያ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም በአዲስ ማሽንና መለዋወጫ ኢንዱስትሪ የሚመረቱ የተለያዩ የመለዋወጫ ምርቶች የአመራረት ሂደትን፤ ለተለያዩ ፋብሪካዎች የሚውሉ የሮለር ምርቶችን፤ የፍሬን ሸራ ምርቶችን የተለያዩ የኢንዱስትሪውን ምርቶች ጎብኝተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪ የሚመረቱ የተለያዩ ፓይፖችን፣ የፕላስቲክ ምርቶችን እና ከፍተኛ የማምረት አቅም ያላቸውን ማሽኖችን ጎብኝተዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኮ/ል ሸጋው ሙሉጌታ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
የሚታዘዙ የስራ ትእዛዞችን በጊዜ እና በጥራት ለማምረት እንደሚሰሩ ገልጸው ግንኙነቱን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ የስምምነት ማዕቀፎች እንደሚዘጋጁ ተናግረዋል፡፡
የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሁንዴሳ ደሳለኝ በበኩላቸው ግሩፑ ራሱን ሪፎርም በማድረግ እያካሄደ ያለው የሪ ብራንዲንግ ስራ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢንዱስትሪዎቹ የሚመረቱ ምርቶች በኮርፖሬሽኑ ስር ለሚገኙ ተቋማት አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የሁለቱ ተቋማት ግንኙነትን ከምርቶች ግብይት በላይ መሆን አለበት ያሉ ሲሆን፤
በስልጠና፣ መልካም ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ፤ በጆይንት ቬንቸርና በተለያዩ መስኮች መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ሁለቱም ተቋማት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስር የሚገኙ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ናቸው፡፡












