በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ከኪሳራ በመውጣት ወደ ትርፍማነት መምጣቱ ተገለፀ::

ሐምሌ13/2015 ዓ.ም(ደብረብርሃን )
የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ከነበረበት ኪሳራ በመውጣት ወደ ትርፍ ተመልሷል ሲሉ የኢንዱስትሪው ዋና ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ረድኤት አባተ ገልፀዋል።
በዛሬው እለት ኢንዱስትሪው የ2015 ዓ.ም አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንዲሁም 2016 ዓ.ም እቅድ ላይ ተወያይቷል።
በውይይቱም ኢ/ር ረድኤት በመጭው በጀት አመት በዋነኝነት በዕውቀትና በስነምግባር የታነፀ ሰራተኛን በማፍራት በኢንዱስትሪው ግንባታዎችን ለመጀመር፣ፕሮጀክቶች ለማስፋፋት፣ የሎደር ምርትን ለማስጀመር ብሎም አዳዲስ ምርቶችን ከቱርክና ጣሊያን ካምፓኒዎች ጋር ውል በመግባት ለመጀመር አቅጣጫ መቀመጡን ገልፀዋል።
በተለይም ኢንዱስትሪው ከውጭ የሚገቡ ማሽነሪዎችን በሃገር ውስጥ እንዲመረት ማድረግ አቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም ሰራተኛው በቁርጠኝነት እንዲሰራ አሳስበዋል።
ኢንዱስትሪው የኮንስትራክሽን ማሽነሪ የሆኑትን ስካቫተር፣ሎደር፣ክሬሸርና ባቺንግ ፕላንት  እንዲሁም ለግንባታ ስራ የሚውሉ ዘመናዊ የፎርም ዎርክ፣ስካፎልዲ ማሽነሪዎችን የሚያመርት ነው።
በበጀት አመቱም መልካም አፈጻጸም እንዲያስመዘግብ  ላበረከቱ ለኢንዱስትሪው አካላት፣ለደብረብርሃን ከተማ መስተዳድር ፣ለጠባሴ ክ/ከተማ ፣ ለጠባሴ ክ/ከ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ የዕውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቷል።
በእለቱ ከውይይቱ ባሻገር ደም የመለገስ መርሃግብር ተካሂዷል።
አንድም እናት በደም እጦት መሞት የለባትም በሚል መርህ የኢንዱስትሪው አመራሮችና ሰራተኞች እንዲሁም የደብረብርሃን ጠባሴ ክፍለ ከተማ አመራሮች ተሳትፈዋል።
የደብረብርሃን ጠባሴ ክ/ከ ስራ አስኪያጅ ኢንዱስትሪው በዘርፉ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ባሻገር በአካባቢያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ለሚያደርገው አስተዋፅዎ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *